የውትድርና ህይወት
የጥቁር አንበሳ - የጀግንነት ውርስ
ክፍል-1
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሚያዚያ 06 ቀን 2017 ዓ.ም
የእናት ሀገር ፍቅር ውስጣቸው የሚንቀለቀል ደመ - ሞቃት ኢትዮጵያዊ ጀግኖች እዚህ ስፍራ የተገኙት ለአላማ ነው። ያሰባሰባቸው ብርቱ ጉዳይ አለ። ስፍራው ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማ አካባቢ ነዉ ። እንዴት እደፈራለሁ የሚል ኩሩ የኢትዮጵያዊነት ስብዕና የቀሰቀሳቸው ወጣቶች፤ ጦር የሰበቀባቸውን ጠላት ለመመከት ወኔ አልቸገራቸውም። ገድሎ ለመሞትም ይሁን ተዋግቶ ለማሸነፍ ፅናት አላጡም። ይልቁንም አደራጅቶ የሚያዋጋቸው መሪ ይፈልጉ ነበር።
እናም የወቅቱን ወጣቶች ክፍተት የሚሞሉ የገነት ጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዙር ተመራቂ መኮንኖች በስፍራው ደረሱ። ሰኔ 19 ቀን 1928 ዓ.ም "ጥቁር አንበሳ" በሚል ስያሜ የሀገር አለኝታና የህዝብ መከታ የሚሆን ማህበር አደራጅተው ፋሽስት ጣሊያንን በቁርጠኝነትና በጋራ ለመፋለም ቃለ መሃላ ፈፀሙ።
በውስጣቸው ከሀዲ ቢኖር እስከ ሞት ሊቀጡ ፣ ከመሀላቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ጠላት እጅ የመውደቅ አደጋ ቢገጥም ቀድሞ ራስን ለማጥፋት ተስማሙ፣ ቃላቸውንም ላያጥፉ እርስ በእርሳቸዉ ተማማሉ ።
የሀገር ዳር ድንበር መደፈር ያንገበገባቸው ወጣቶች፣ የህዝብ ሉአላዊነት መነካት ያስቆጣቸው መኮንኖች በመሪና ተመሪ ተደራጅተው ወደ መሀል ሀገር የዘለቀውን የፋሽስት ጦር መውጫ መግቢያ አሳጡት። ሰኔ 20 ቀን 19 28 ዓ.ም ወለጋ ነቀምት ከተማ ልዩ ቦታው "በኬ ቦንያ " አካባቢ ነው።
የኢትዮጵያ አርበኞች ከፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ጋር በወለጋ ተራራ እና ሸንተረሮች ላይ እየተፋለሙ ይገኛሉ። ጠላት ነቀምት ላይ ማዘዣውን በማድረግ በግንባር ለሚዋጋው ኃይሉ የውጊያ ድጋፍ ይሰጣል። የጥቁር አንበሳ ጀግና መኮንኖች የውጊያውን ኃይል ማዛባት እንዳለባቸው የገነት ጦር ትምህርት ቤት ስልጠናቸው አስታወሳቸው። በአጭር ጊዜ አቅደው ለትግበራ ተዘጋጁ። የጠላትን ስነ-ልቦና ለመስለብና ድል ለመቀዳጀት የጠላትን የስህበት ማዕከል ለዩ ። ማዘዣና አየር ኃይሉን ማጥቃት እንዳለባቸው ወሰኑ። በከፍተኛ የሰው ኃይልና በዘመናዊ መሳሪያ የሚጠበቀውን የጠላት ማዘዣና የአየር ኃይል ማጥቃት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተውታል። ይሁን እንጂ "ምንም አይነት መስዋዕትነት ከሀገር በላይ አይሆንም " የጥቁር አንበሳዎች መርህ ነበር።
በዚሁ ቀን በልዩ ወታደራዊ ጥበብ እና በፍፁም የሀገር ፍቅር ወኔ የተሞሉት የጥቁር አንበሳ ጀግኖች ወደ አየር ኃይሉ በመገስገስ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘሩ። በእጃቸው የያዟቸውን ቦንቦች እየወረወሩ አውሮፕላኖችን በማጋየት ሊከላከል የሞከረውን የፍሽስት ጦር በጥይት እየቆሉ ቅፅበታዊ ማጥቃታቸውን ሰነዘሩ ። ድንገት ግቢውን የእሳት ረመጥ አድርገው ውስጡን በጭስ ሸፈኑት ። መግቢያ መውጫ ያጣውን ጠላት ከብበው አደባዩት። ጠላት በወረራ በያዛቸው ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዲህ አይነት ውጊያ ገጥሞት የሚያውቅ አይመስልም።
ጠላት ይሆናል ያላለው ሲሆን ፣ ያላሳበው ሲፈፀም ወኔው ተሰልቦ የእውር ድንብሩን ብቻ ለመከላከል ሞከረ። የገጠመው ከኢትዮጵያዊ የጥቁር አንበሶች ነውና ሊሆንለት ግን አልቻለም። ጀግኖቹ ኢላማቸውን እየለዩ ፣ የጠላትን ቁስ በማውደምና የሰው ኃይሉን በመደምሰስ በአጭር ሰአት ግዳጃቸውን መፈፀም ቻሉ። በስፍራው የነበሩ 3 አውሮፕላኖች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ፓይለቶችን ጨምሮ 13 ከፍተኛ መኮንኖች እና የጠላት ወታደሮች ተገደሉ። በዚህ ልዩ ዘመቻ የጥቁር አንበሳ ተዋጊዎች የአሸናፊነት ስነ- ልቦና ሲገነባ የጠላት ሞራል በእጅጉ ሊላሽቅ ቻለ።
ዘመቻው ኢትዮጵያ ለጠላት የማትመች ፣መሬቷም ረመጥ መሆኗን ለፋሽስቶች መልዕክት ያስተላለፈ ክስተት ሆነ። የጥቁር አንበሳውን ጦር እየመሩ ይህንን ልዩ ዘመቻ በስኬት የፈፀሙት የገነት ጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ኮርስ ተመራቂ ሌተና ኮሎኔል በላይ ኃይለአብ ነበሩ።
የወቅቱ የገነት ጦር ትምህርት ቤት በሌላ መጠሪያም የሚታወቅ ቢሆንም ዛሬ ግን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሚል ተሰይሟል። የዚህ ፅሁፍ የቆይታችን ማስታወሻ "የጥቁር አንበሳ አንባ" የሆነው የቀድሞው ገነት ጦር ትምህርት ቤት የዛሬው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ነው።
የዛን ወቅት የፀረ-ፋሽስት ወረራ ተጋድሎ ጀግና መኮንኖች መፍለቂያ ግቢ የተገኘሁት ለስልጠና ነው። እኔና ከመላው የሠራዊታችን ክፍሎች የተውጣጡ የሠራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ አመራር እና የሚዲያ ሙያተኞች ነን። ስልጠናችን በዚህ የጀግኖች መፍለቂያ መሆኑ ለግባችን ስኬት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በጥቁር አንበሳ ጀግኖች ስነ-ልቦናችን እየተገነባ፣ በደማቅ ገድላቸው ትውስታ መንፈሳችን እየረካ ፣ እንደ እነርሱ በፈተና ፀንተን የሀገር ኩራት ተተኪዎችን በአምሳላችን የምንቀርፅበትን እድል እንደሚኖረን አልተጠራጠርንም።
ዛሬ የጥቁር አንበሳ ጀግኖቹ በዚህ ግቢ አይኑሩ እንጂ መንፈሳቸው አልጠፋም። ታሪክና ገድላቸው በግቢው አየርና በሰው ላይ ሰፍሮ ጀግንነትን ያወርሳል። አንድነትን ፈጥሮ ውስጥን በሀገር ፍቅር ይሞላል። በእርግጥም የጀግንነታቸው ምንጩ ፣ የድላቸው ምክንያቱ ቢዳሰስ አንድነትና የሀገር ፍቅራቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም። እኛም እዚህ የተገኘነው በአንድነት ነበር። ለአንድ አላማ ስኬትና ግብ። እናም እኔ እያልኩ ሳወጋ የስልጠናው ተካፋዮችንም ጭምር እያልኩ መሆኑ ይያዝልኝ ። ሠራዊታችንም እንዲሁ ተልዕኮና ህይወቱ የጋራ ነው፣ የግልና የተናጠል ግዳጅና ግብ አይኖረውም። ግዳጁ አንድ ፣ ግቡም የጋራ ነው። እኔም የጥቁር አንበሳ መፍለቂያ ካምፕ ቆይታዬን ሳካፍል ብዙውን እንደ አንድ በመቁጠር ነው።
የምስረታ ስሙ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሲሆን ዛሬ ላይ በአካዳሚነት አድጎ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የሚል ስያሜን አግኝቷል። የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ መገኛ ሆለታ ገነት ነው። ከመዲናችን አዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር አካባቢ ይሆናል። ወደ ሆለታ ገነት በምዕራብ አቅጣጫ በሁለት በኩል ከአዲስ አበባ መውጣት ይቻላል።
በቀድሞው ርቀቷ 44 ኪሎ ሜትር ተጉዘህ ወደ ግራ ስትታጣፍ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ "እንኳን ደህና መጡ" ብሎ ይቀበልሃል። እኔ ግን አዲስ አበባ የደረስኩት ከ500 በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጭ ነው። መነሻዬ ለህዝብና ለሀገር ሰላም መከበር ቀን ከሌት ከፅንፈኞች ጋር ከሚፋለሙ ጀግኖች ስፍራ ነው።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የመግቢያውን በር ስዘልቅ ረዥም ሀውልት ተመለከትኩ። የሀውልቱ አናት ላይ በሰማይ እንደሚበር እርግብ የወታደር ምስል አለው። ከዚህ ቀደም ይህንኑ ሀውልት በአካልም በፎቶም አውቀው ነበር። ስለ ሀውልቱ ቅድመ-ታሪክ የሚያስረዳኝ ባልማግኘቴ ዛሬም ድረስ ጥያቄው ውስጤ አለ።
ከዚያስ ይቀጥላል......
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0