በ3 ሀገራዊ ቋንቋዎች የመንጃ ፈቃድ ስልጠና እንዲሰጥ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ እና ሶማልኛ ቋንቋዎች የመንጃ ፈቃድ ስልጠና እንዲሰጥ መፈቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
ባለሥልጣኑ በሪፎርም ሒደት ውስጥ እንደሚገኝ እና ለረጅም ግዜ ሲጠየቁ የነበሩ በርካታ የተገልጋዮቻችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየፈታ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ተቋሙ ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች ውስጥ አዲስ መንጃ ፍቃድ አገልግሎት አንዱ ሲሆን÷ የእጩ አሽከርካሪዎች የንድፈ ሃሳብ ስልጠና እና ፈተና በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሲሰጥ እንደነበር ተጠቅሷል።
በአፍ-መፍቻ ቋንቋቸው በአማራጭነት ቢሰለጥኑ እና ቢፈተኑ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረ የመልካም አስተዳድር ጥያቄ መሆኑን የባለስልጣኑ መረጃ አመልክቷል፡፡
ይህን ተከትሎም ተቋሙ በዝርዝር ጉዳዩን ፈትሾ የአካታችነት ጥያቄው አሳማኝ መሆኑንና የተሟላ የካሪኩለም ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን በማንሳት ለመንጃ ፍቃድ ስልጠና በ3 ሀገራዊ ቋንቋዎች ስልጠና እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም ፍቃድ ከሰጣቸው 137 ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ከአማርኛ በተጨማሪ በአፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ እና ሶማልኛ ቋንቋዎች ለማሰልጠን ፍቃደኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ስለሆነም ሞዴል ተቋማት ለሆኑ 12 ማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃድ መሰጠቱ ነው የተጠቆመው፡፡
በሌላ በኩል ዕጩ አሽከርካሪዎች ከአማርኛ በተጨማሪ በቀረቡት የቋንቋ አማራጮች መሰልጠን እና መፈተን እንደሚችሉ ባለስልጣኑ አስገንዝቧል፡፡